እውነት ለመናገር አፈሩን ያቅልለትና የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትራችን መለስ ዜናዊ ያስባት የነበረችውን ኢትዮጵያ ብዙ ጊዜ አስቤም ቢሆን ልስማማበት ይቸግረኛል። ያው እንደተለመደው ተቀበል ካልተባልሁ በስተቀር። አሁን እየታጨደ ያለውን ቢያይ እሱም ቢሆን ለመቀበል የሚቸግረው ነው የሚመስለኝ።
የህዳሴ ግድብን ሳስብ ግን ምናልባትም መለስ በኢትዮጵያ ታሪክ ከሚታወስባቸው ጠንካራ ጎኖች አንዱና ዋነኛው ይመስለኛል። እንደነ ሚኒሊክ አመድ አፋሽ ካላደረግነው በስተቀር። በዜሮ ማባዛት ልማድ ስለሆነ።
ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ መሰረቱን ያስጣለው ብሎም እስከ ሂወተ ህልፈቱ ድረስ በሚገባ ስራውን የመራው አሁንም በጠንካራ አመራሮች ስራው የቀጠለው የህዳሴ ግድብ ከቀጥተኛ ግቡ ባሻገር ኢትዮጵያውያንን ምን ያህክል በትልልቅ አገራዊ አጀንዳዎች መያዝ ይቻል እንደነበር ያመላክተኛል። ካሳለፍናቸው አላስፈላጊ አድካሚ ጊዜአዊና ጥቃቅን ሀሳቦችና ተግባሮች በተቃራኒ እንደሆነ ይሰማኛል።
ያሳለፍናቸውን የቀርብ ጊዜ የግብጽ እውነታዎችን ሳስብ ከህዳሴ ግድብ ባሻገር ሌሎች ፕሮጀክቶችን እንዳስብ አስገደደኝ። አንዱም ህዳሴ ከተማን መገንባት ነው። ለዛውም ኢትዮጵያውነትን የበለጠ የሚያጠናክር በህዳሴ ግድብ ምክንያት ከቦታችው የተፈናቀሉ ዜጎችን ግምት ውስጥ ያስገባና ተጨማሪ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያለው ዘመናዊ ከተማ። ከህዳሴ ግድብ ጎን። ምኞት አይከለከል።
እየተገነባ ያለው ግድብ ግዙፍ ነው። እናም የግድቡ ግብ ምንም እንኳን እሱም እጂግ
አስፈላጊ እንደሆነ ብረዳም ኤሌክትሪክ ማመንጨት ብቻ መሆን አለበት ብየ አላምንም። የቱሪዝም ሀብት ምንጭ መሆን አለበት። የዓሳ
እርባታ ምንጭና ሌሎች ውሃውን በብዛት የማይጠቀሙ( ውሀውን አላዛኝ ለሆነችው ግብጽ እና በዚህ ውስብስብ በሆነ ወቅት ከጎናችን ላልተለየችን
ወዳጃችን ሱዳን ይሁን ብየ ነው) የኢኮኖሚ አማራጮች መታሰብ እንዳለባቸው ይሰማኛል። ህዳሴ ከተማን በቅርብ ርቀት መገንባት ይህን
የኢኮኖሚ አውድ ለማስፋት እንደሚያግዝ ይሰማኛል።
የግብጾች የተጠናከረ የተንኮል ዘመቻ እኛ ኢትዮጵያውያን ሌላ ቁም ነገር እንዳናስብ ማድረግ ነው። እኛ ግን ለእነሱ ዘመቻ መልስ በመስጠት ከመጠመድ ባለፈ እራሳችን አስበን እንደ ህዳሴ ግድብ በራሳችን መንገድ ድካማቸው ውሃ የማይቋጥር መሆኑን ማመላከት የሚገባ ይመስለኛል።
በግብጾች መንገድ ልክ እንደ ካይሮ ወይንም አሌክሳንድሪያ ከተሞች ዘመናዊ የሆነ ህዳሴ
ከተማን የራሳችን በሆነው አባይ ወንዝ ላይ ቆርቁረን እነሱንም ለንግድና ለሽርሽር ብንጋብዛቸው ይቻላል ብየ አልማለሁ። ምኞት አይከለከል።
ግድቡማ ተገደበ። ክብርና ምስጋና ለኢትዮጵያ ልጆች ይሁንና። እስከነ ግድፈታቸውም
ቢሆን።
ህዳሴ ከተማን እንቀጥል።
Comments