አንዳንድ ወገኖች እየሆነ ባለው አስከፊ ክስተት ተስፋ የመቁረጥ ዝንባሌ ይታይባቸዋል። መሪዎችም ጭምር እንዲህ ካልሆነ ስልጣኔን እለቃለሁ እንዲያ ካልሆነ ከእነእንትና ጋር መስራት ያስቸግረኛል ሲሉ ይደመጣሉ። ስልጣን ከለቀቅህማ ፎርፌ ሆነ ማለት ነው። የሴራ ፖለቲካ በነገሰበትና ብቁ ተቋም ባልተገነባበት ሁኔታ ከትግሉ በራስህ ፈቃድ ወጣህ ማለት ለውጡ ወደማትፈልገው መስመር በነጻነት እንዲጓዝ ፈቀድህ ማለት ነው። ባይሆን ቦታውን ካንተ/ካንቺ በተሻለ ሊታገል የሚችል ሰው ተክተህ/ተክተሽ የራስህን/የራስሽን ቦታ መፈለግ ብልህነት ነው።
እኔ አሁን ኢትዮጵያ ለገባችበት ቅርቃር አንዱ ምክንያት ከዓመታት በፊት በነበረው ተመሳሳይ የለውጥ ወቅት በጊዜው የነበሩ ሰዎች በተለይ ደግሞ ባለስልጣናትና ሹመኞች የወቅቱን ሴረኛ ቡድን በተሻለ ሃሳብ መታገልና መመከት ያለመቻላቸው ውጤት እንደሆነ ነው የማስበው። ግማሾቹ ሃሳቡ ሳይስማማቸው ሲቀር እየወጡ ቀሪወቹ ደግሞ በተናጠል ሲመቱ ወይም ሲታሰሩ ሌላው ቆሞ እያየና መድረኩን በፎርፌ ለቆ ነው እዚህ የደረስነው። ቢያንስ አንድ ሁለተኛ ተመጣጣኝ የፖለቲካ ሃይል ተገንብቶ ቢሆን ኖሮ አይደለም ኢትዮጵያን አሁን የጥፋት ሃይል ተብሎ የሚሳደደውንም እንታደገው ነበር።
የቅርቡን የህውሃትን ገጠመኝ እንደምሳሌ ብንወስድ እንኳን ለዚያ ሁሉ ስጋታቸው ምንጭ ከአዲስ አበባ ፖለቲካ እራሳቸውን አግልለው መቀሌ መከተማቸው ይመስለኛል። አብረው መታገል እየቻሉ ፎርፌ ሰጥተው ነው እራሳችውን በዚህ ሁኔታ ውስጥ ያገኙትና እንደ ሀገርም አላስፈላጊ መስዋእትነት የከፈልነው። ቀሪወቹም ከዚህ መማር የግድ ይላቸዋል። ደግሞስ ለውጥ ጀምሮ ማን እንዲጨርሰው ነው የምንጠብቀው። እርግጥ ሰው ሞቷል። ለዚያውም በአሰቃቂና ምንም ለጉዳዩ እውቅናም ሆነ ግንዛቤው የሌላቸው አፈር ገፊ ምስኪኖች።
በዚህ ሰዓት ከለውጥ እራስን ማግለል ማለት በዱር በገደሉ እየተንከራተቱ የህይወት ዋጋ የሚከፍሉትን መለዮ ለባሾችን ክብር ማሳነስ ብቻ ሳይሆን ተጨማሪ መስዋእትነትን መጋበዝ እንደሆነ ነው የሚሰማኝ።
ልዩነትን በተሻለ ሃሳብ ሞግት። የሆነ ሴረኛ ቡድን የግፉ አካል ነው ብለህ ካሳብክ መርምርና በማስረጃ አስደግፈው
ለሚመለከተው አሳውቅ፡ ሞግት።
''ጠላት በሕዝቡ ውስጥ የቀበረው፣ የዘራውና የበተነው ብዙ መቅሰፍት አለ። አንዳንዱን መዋቅራዊ አድርጎታል፤ አንዳንዱን የሕግ ቅርጽ ሰጥቶታል፤ ለአንዳንዱ ሥርዓት ሠርቶለታል፤ ሌላውን በትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ አካትቶታል፤ ለአንዳንዱ በዓል ሰይሞለታል፤ ለሌላው ሚዲያ አዘጋጅቶለታል። ለአንዳንዱ ተቋም አቁሞለታል። አንዳንዱ የሕዝቡ ትርክት ሆኗል፤ ሌላው በዘፈን ውስጥ ገብቷል፣ ሌላውም የፓርቲ ፕሮግራም ሆኗል። ይሄን ሁሉ ዱካ በዱካ እየተከተልን የዕዳ ደብደቤውን መደምሰስ ይጠበቅብናል''። ከአብይ አህመድ( ጠሚ)፣ ከ 2013 የከተራና የጥምቀት በዓል ምኞት መግለጫ የተወሰደ።
ከምንም በላይ ህዝብን ከጎንህ አድርገህ ታገል። ወደኋላ ለማለት አሁን ጊዜው አይደለም። እንዲያውም ባይገርምህ አሁን ለውስጡ ሳይሆን ለውጩም ሲባል ሁላችንም በንቃት የምንቆምበት ጊዜ ላይ ነን። ሀገር መቀጠል አለባትና።
መልካም።
Read More:
Aligning Ethiopian Energy Markets for Innovation and More Jobs
Be bold to embrace It!
Do Subscribe to Showing Up ^ Exposure Matters to Receive Updates by Email
Comments